Skip to main content
belayineh

ለመቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ የዕውቅናና በህይወት ታሪኩ ዙሪያ የተፃፈ መፅሀፍ የማስተዋወቂያ መድረክ በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል። በስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ መቶ አለቃ በላይነህ ዲንሳሞ ለአገሩ ባስገኘው ድል ታሪክ ሲያወሳው ይኖራል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በገለፃቸው የዛሬው መድረክ የሲዳማ ዕንቁ ልጆች ለአገሪቷ የነበራቸውን አስተዋጽኦ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው በማለት ለአገሪቷ የደከመና የተጋ እንደማይረሳም ጭምር ለማሳየት ነው ብለዋል። መቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዲንሳሞ ከክልላችን የተገኘ ዕንቁ በመሆኑ እንኮራለን ብለዋል።

በክልላችን የምትገኙም ሌሎች አትሌቶች በዓለም መድረክ ተገኝታችሁ እያሳያችሁ ያላችሁት ውጤት የሚያኮራ ነው በማለት እንደ መቶ አለቃ አትሌት በላይነ ዲንሳሞ በፅናት መጓዝ ይገባችኋል ብለዋል።

መቶ አለቃ አትሌት በለይነህ ዲንሳሞ እንደገለፁት በአዲስ አበባ በተካሄደው የመፅሐፍ ምረቃ ላይ ተገኝተው ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባደረጉት ንግግር በወዳጆቼ ፊት ከፍ ያደረገኝ ነው በማለት አመስግነዋል። ለሰላሳ አራት ዓመታት ተረስቼ ቢሆንም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታውሰው በዚህ መልኩ በትውልድ አከባቢዬ ዕውቅና ስለሰጡኝ ላቅ ያለ ደስታና ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል።

በስነስርዓቱ ላይ በመቶ አለቃ አርቲስት በላይነህ ዲንሳሞ የተፃፈውን መፅሀፍ የክልሉ መንግስት ከ6 ሚሊዮን ብር ግዢ እንደሚፈፅም የገለፀ ሲሆን ለአትሌቱ በሀዋሳ ከተማ የ1ሺ ካሬ መሬት እንደሚሰጠው ተገልጿል።

ለአትሌት ቱርቦ ቱሞ ቤተሰብም 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በዕለቱ ለተገኙ ለአገሪቱ ሜዳልያ ላስገኙ የክልሉ አትሌቶች የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።

የሲዳማ ብ/ክ/መ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት

ግንቦት 12-2015 ዓ.ም

ሀዋሳ