ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ
መልዕክት
የሲዳማ ህዝብ ለረዥም ዘመናት ሲያደረግ የነበረዉ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከረጅም ዘመን እልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋዕትነት በኃላ ፍሬ አፍርቶ የሲዳማ ህዝብ በክልልነት በመደራጀት 10ኛዉ የፌዴሬሽኑ አባል ክልል የሆነ ሲሆን የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የአደረጃጀትና የመዋቅር ስራዎችን በማጠናቀቅ የህዝቡን የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን እንዲሁም ለዘመናት የቆዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲያስችለዉ የ10 ዓመት መሪ ክልላዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ባደረገዉ ርብርብ በርካታ ድሎችን ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡
በዚሁ መነሻ የክልሉ መንግስት የክልሉን የመልማት አቅም አሟጦ በመጠቀም የህዝቡን ተጠቃሚነት በላቀ መልኩ ለማረጋገጥና በሁሉም መስክ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የክልሉን ነዋሪ በቤተሰብ ደረጃ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥና ዘላቂነት ያለዉ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ በመረባረብ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ መልኩ በክልሉ ለኢኮኖሚና ማሀበራዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በሁሉም አከባቢ ፍትሃዊነት ያለዉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በጥራትና በፍጥነት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የክልሉ መንግስት በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም ለጤናዉ መስክ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን እንዲሁም ጥራት ያለዉ የትምህርትና ስልጠና መስኮችን በማስፋፋት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን እንዲወጡ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የክልሉን ህዝብ ቱባ ባህልና እሴት በመጠበቅ እንዲሁም የክልሉን የቱሪዝም ሀብቶች በአግባቡ በማስተዋወቅና በማልማት ክልሉ ከዘርፉ ተገቢዉን ጥቅም እንዲያገኝ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን በአጠቃላይ ክልሉን ለስራና ኢንቨስትመነት ተመራጭ ለማድረግ ዘለቂነት ያለዉ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ በማድረግና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዜጎች መብቶቻቸዉ ተጠብቀዉ ያለምንም ስጋት በሰላም የሚኖሩበትን ሰላማዊ ክልል ለመገንባት በርካታ አኩሪ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን አሁንም የመልካም አስተዳደር የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ በመተግበር የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ ብልሹ አሰራሮችንና የሌብነት ተግባራትን በመታገል የነዋሪዉ እራካታን ለማሳደግ ጠንካራ አመራር በመስጠት ተግቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በመሆኑም መላዉ የክልላችን ነዋሪ የክልሉ መንግስት ያቀደቸዉ ዕቅዶች በሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆኑና የሀገራችንና የህዝቦቿን የብልጽግና ጉዞ እዉን ለማድረግ በሚያደረገዉ ዘርፈ-ብዙ ርብርብ ከክልሉ መንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪዉን ያቀርባል፡፡